What's Happening‎ > ‎

ወገን ለወገን

posted Dec 22, 2014, 3:21 AM by Haile Sellassie Kebede

 


የኢትዮጵያ የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማህበር

የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ክፍተትን በማጥበብ ልማትን ለማፋጠን የሚሠራ ድርጅት

1.  አጠቃላይ መረጃ

 

1.1   የማህበሩ ሕጋዊ ሰውነት

የኢትዮጵያ የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማህበር በ1994 ዓ/ም የተቋቋመና ከ2001 ዓ/ም ጀምሮ በአዋጅ 621/2001 መሠረት የኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጎ አድራጎት ድርጅት ተብሎ በመታወቂያ ሠርትፊኬት ቁጥር 0618 ዳግም ተመዝግቦ በትምህርት፣ በጤና፣ በስልጠና በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በሰው ኃይል ሥልጠና ላይ በማተኮር የሚሠራ  ሀገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅት ነው፡፡

1.2 ዓላማ

የማህበሩ ዓላማ በዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር  አማካይነት ለልማት የሚጠቅሙ የተለያዩ ሳይንሳዊ ግኝቶችን፣ ቴክኖሎጂዎችንና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን፣ የሌሎች ሀገሮች ልምዶችን፣ ምርጥ ተሞክሮዎችንና እንዲሁም የማቴሪያል፣ የቴክኒክና ፕሮፌሽናል ዕርዳታዎችን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች በዕርዳታ በማስመጣት፣ በማስረጽና ከሀገራችን ተጨባጭ ፍላጎት ጋር አዛምዶ ተግባራዊ በማድረግ የመንግሥትንና የኅብረተሰቡን የልማት ጥረት ማገዝ፣ ነው፡፡

1.3. ራዕይና ተልዕኮ

 

የማህበሩ ራዕይ ‹‹ሀገራችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ የመጠቀች በኢኮኖሚ የዳበረች ኢትዮጵያን ማየት›› ሲሆን ይህ ራዕይ ይሳካ ዘንድ የማህበሩ ተልዕኮ ‹‹በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የልማት መ/ቤቶችና ድርጅቶች፣ በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያ፣ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ለጋሾች፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ጋር በመተባበርና በማስተባበር የማቴሪያል፣ የቴክኒክና፣ የቴክኖሎጂ ድጋፍና ትብብር  እንዲሁም የማቴሪያል ዕርዳታ የምታገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸት›› ነው፡፡

 

1.3  የትኩረት መስኮች

 

የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዓላማው ይሳካ ዘንድ ማህበሩ አምስት ቁልፍ የልማት ዘርፎችን መርጦአል፡፡ እነርሱም ጤና፣ ትምህርት፣ የሰው ኃይል ግንባታ /ሥልጠና/፣ ግብርናና ኢንዱስትሪ ናቸው፡፡

 

1.4 አበይት ክንውኖች /ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች/

 

በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የልማት  ድርጅቶችና መ/ቤቶች፣ በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ     ኢትዮጵያውያን፣ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ለጋሾች፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ጋር በመተባበርና በማስተባበር ባደረገው ጥረት የሚከተሉትን ተግባራት ለማከናወን ተችሎአል፡፡ 

 

 

1.4.1  የትምህርት ድጋፍ ፕሮግራም /Education Support Program/

 

የፕሮግራሙ ዓላማ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞችን ጨምሮ በትምህርት ቤቶች የሚያስፈልጉ መማሪያና ማስተማሪያ እንዲሁም ማጣቀሻ መጻሕፍት፣ ኮምፑዩተሮች፣ የላቦራቶሪ መሣሪያዎች፣ ለትምህርቱ ጥራት መሻሻል የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ በዕርዳታ የሚገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት ሲሆን በፕሮግራሙ ሥር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ አጋር ድርጅቶችን በማፈላለግ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የማቴሪያል ድጋፍ ማሰባሰብ ተችሎአል፡፡

 1.4.2  የመጻሕፍት ድጋፍ ፕሮጀክት(Books for Schools Project)

 

በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ ግብአቶች መካከል መጽሐፍት ከመምህሩ ቀጥሎ የሚጠቀስ ወሳኝ ግብዓት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ይህ ብቸኛ የሆነውን የትምህርት ግብዓት የማያሟላ ትምህርት በጥራት ይሰጣል ተብሎ አይታመንም፡፡

 

በዚህ መሠረት፣ ማህበሩ በአሜሪካ፣ በካናዳና በእንግሊዝ ሀገር ከሚገኙ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች እና በነዚህ ሀገራት ከሚኖሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ማህበራትና ግለሰቦች ጋር ግንኙነት በመፍጠር እስካሁን ከ 1,755,000 መጻሕፍት አሰባስቦ በማስመጣት ለትምህርት ቤቶችና ተቋማት አከፋፍሎአል፡፡ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት፣ የወጣት ማህበራት በትምህርትና ስልጠና ዙርያ የሚንቀሳቀሱ ሀገር በቀል ድርጅቶች ወ/ዘ/ተ ናቸው፡፡

 

1.4.3 የኮምፑዩተር አቅርቦት ፕሮጀክት /Computers for Schools Project/

 

ይህ ፕሮጀክት የትምህርትን ጥራት ለመስጠበቅ መጽሐፍት በማቅረብ በኩል ማህበሩ የጀመረውን ፕሮጀክት የመደገፍ ነው፡፡ በኮምፒውተር ቴክኖሎጂ የታገዘ ትምህርት ትምህርት ለሚሰጠውም ሆነ ለሚቀበለው ቀላልና ቀልጣፋ ከማድረጉም በላይ በመማር ማስተማሩ ሂደት ሊደርስ የሚችለውን የጊዜ፣ የጉልበትና የማቴሪያል ብክነት በማዳን የትምህርት ስርዓቱ ውጤታማ (efficient) እንዲሆን በማድረግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

 

በዚህም መሠረት ቢያንስ በያንዳንዱ ትምህርት ቤት 10 ኮምፑዩተሮችን የያዘ Mini Computer Lab እንዲኖር ለማድረግ ያተኮረ ፕሮጀክት እ.ኤ.አ በ2006 ዓሕም ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው Bethany Negash Memorial Foundation 1,200 ኮምፑዩተሮች፣ አሜሪካ ከሚገኘው Books For Africa (BFA, USA) 16 ኮምፑዩተሮች፣ አሜሪካ ከሚገኘው EKTTS (USA Office) 460 ኮምፑዩተሮች፣ እንዲሁም እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው Computer Aid International (CAI, UK) 6,712 በድምሩ 7,928 ኮምፑዩተሮችን በዕርዳታ በማስመጣት ችግር ላለባቸው ትምህርት ቤቶችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች አከፋፍሎአል፡፡

 

1.4.4 የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ድጋፍ ፕሮጀክት /Public Library Support Project/

 

እስካሁን ባለው ዕድገት የቤተመጽሐፍት አገልግሎት በትምህርት ቤቶችና ከፍተኛ ተቋሞች ብቻ የተወሰነ ሲሆን ከዚህ ውጭ የሚገኘው ኅብረተሰብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚሆንበት ዕድል አልተፈጠረም፣ ቢኖርም አገልግሎቱ እንደ አዲስ አበባ በመሰሉ ጥቂት ከተሞች የተወሰነ ሆኖ እነሱም ቢሆኑ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ስለሆነም የፕሮጀክቱ ዓላማ ከትምህርት ቤት ውጪ በሚገኘው በተለይም በገጠሩ ኅብረተሰብ ላይ ያተኮረ ሆኖ ዓላማውም በህብረተሰቡ ዘድ የማንበብ ልምድ ለማዳበር ነው፡፡

 

በዚህም መሠረት

1ኛ       ማህበሩ አግባብ ካላቸው የክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች እንዲሁም በየክልሉ ከሚገኙ የልማት ማህበራትና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበርና በማስተባበር ባደረገው የተቀናጀ እንቅስቃሴ በ2004 / በሐዋሳ፣ በ2005 ዓ/ም በባህርዳር፣ በ2006 በመቀሌናጅማ ከተሞች የመጀመሪያዎቹ አራት የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ተመርቀው በአሁኑ ጊዜ አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን በ2007 ዓ/ም በአሶሳና ጋምቤላ ከተሞች ተመሳሳይ አገልግሎት ለመክፈት መጻሕፍት፣ ኮምፑዩተሮችንና ቁሳቁሶችን ማጓጓዝ የተጀመረ ሲሆን በቀጣይ ዓመታትም በሠመራ፣ ጂጂጋ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረርና አዲስ አበባ ከተሞችለሚከፈቱት ቤተ መጻሕፍት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የፕሮጀክት ስምምነት ለመፈራረም ንግግር ተጀምሮአል፡፡

 

የተጠቀሱት የሕዝብ  ቤተ መጻሕፍት እያንዳንዳቸው 10,000 መጻሕፍት 60,000 የኤሌክትሮኒክስ መጻሕፍት፣ (E-books) ለኢንተርኔትና Koha library system አገልግሎት የሚውሉ 23 ኮምፑዩተሮች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ጠረጴዛዎች፣ ሸልፎችና ወንበሮች የቢሮ ዕቃዎች ያሉዋቸው ሲሆን እያንዳንዳቸው ከ5.1 ሚልዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው ናቸው፡፡ ቤተመጻሕፍቱ አገልገሎት መስጠት ሲጀምሩ በየዓመቱ 150,000 በላይ ለሚሆኑ አንባቢያን አገልግሎት እንደሚሰጡ ይገመታል፡፡ 

 

2ኛ/ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ አጋጣሚዎችና ጊዜያት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥርሚገኙ በርካታ የቀበሌ የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ያለባቸውን ከፍተኛ የመጻሕፍት እጥረት ለማቃለል ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ 22,800 በላይ መጻሕፍትማከፋፈል የተቻለ ሲሆን ፕሮጀክቱ ተገቢው ዕውቅና እንዲኖረው በክፍለ ከተማ ከሚገኙ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤቶች ጋር በጋራ በመስራት ላይ እንገኛለን፡፡

3ኛ/ መንግሥት የሕግ ታራሚዎችን አጠቃላይ ዕውቀትና ግንዛቤ ለማስፋት በሁሉም ማረሚያ ቤቶች የቀለምና የሙያ ትምህርት እንደሚሰጥ ይታወቃል፡፡ ማህበሩም በዚህ ረገድ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በመነሳሳት ላለፉት በርካታ ዓመታት 5084 በላይ የመጻሕፍት ልገሳ ያደረገ ሲሆን ከዚያ በፊትም ብር 150,000 ግምት ያላቸው የተለያዩ መጻሕፍትና ከአንድ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅት ጋር በመተባበር 20 ኮምፑዩተሮች እንዲያገኙ ሁኔታዎችን አመቻችቶአል፡፡

4ኛ/  ሆስፒታሎች ከህክምና ባሻገር የህክምና ትምህርት በመስጠት በርካታ ሀኪሞችና የህክምና ባለሙያዎች የሚያሰለጥኑ እንደ መሆናቸው መጠን መታገዝ እንዳለባቸው በማመን በቅድሚያ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ አጠቃላይና ሪፈራል ሆስፒታሎች መካከል ሦስቱን በመምረጥ በየጊዜው የሕክምና መጻሕፍት ዕርዳታ እያደረገ ሲሆን በቀጣይ በክልል የሚገኙ ሆስፒታሎች የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ለማድረግ በውጭ ሀገር ከሚገኝ ለጋሽ ድርጅት ጋር በመነጋገር ላይ ይገኛል፡፡

5ኛ/ እስካሁን በተደረገው ጥረት 950 የሚሆኑ ምርጥ የህክምና መጻሕፍት የለገሰ ሲሆን ቀደም ሲልም በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የማህበራችን ጽ/ቤት በሰሜን አሜሪካ ከሚገኘው ENAHPA ከተሰኘ የሕክምና ባለሙያዎች ማህበር ጋር በመተባበር ለጎንደር፣ ለአዲስ አበባና ለጂማ ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥራቸው 98,895 የሆኑ የተለያዩ ህክምና መጻሕፍትና የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶች  እንዲያገኙ ከፍተኛ የማስተባበር ሥራ አከናውኖአል፡፡

6ኛ/ ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ ከፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከሰሜን አሜሪካ የሕክምና ባለሙያዎች ማህበር ENAHPA ጋር በመተባበር ከ35 በላይ የህክምና ዶክተሮች በበጎ ፈቃደኛነት ወደ ኢትዮዽያ ሲመጡ ማህበሩ እነዚህ የህክምና ባለሙያዎች ያመጡዋቸውን ሁለት ኮንተይነር የህክምና መሣሪያዎችና ቁሳቁሶችን ለማጓጓዝ የተጠየቀውን ሙሉ ወጪ ከመሸፈኑም በላይ ሐኪሞቹ በአየር የተጓጓዙበትን ግማሽ የትኬት ዋጋ ብር 281,000 ሸፍኖአል፡፡

 

 

2   በፕሮጀክት አፈጻጸም የህብረተሰብ ተሳትፎ አስፈላጊነት

 

ማህበሩ በትምህርት፣ በጤና፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር የጀመረው ጥረት ሠፊ ሀገራዊ እንደምታ ያለው ከመሆኑ ባሻገር ውስብስብና ቀላል የማይባል ወጪ እንደሚጠይቅ ይታመናል፡፡ እስካሁን ባለው ጥረት ቀላል የማይባል ሀገራዊ ተሳትፎ ያለ ቢሆንም በውጭ ከሚገኘው ዕርዳታ ጋር ሲታይ ግን ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ ማህበሩ ባደረገው ጥረት እስካሁን ወደ ሀገራችን የገባው የመጻሕፍት፣ ኮምፑዩተሮችና ተዛማጅ ቴክኖሎጂዎች በገንዘብ ሲገመት ከ50 ሚልዮን ዶላር በላይ መሆኑ የአባባሉን ትክክለኛነት ይገልጻል፡፡ ይሁንና እስከ መቼ ድረስ በውጭ ድጋፍ እንንቀሳቀሳለን? እኛ ለኛ መንቀሳቀስ የምንጀምረው መቼና እንዴት ነው? የሚለው ጥያቄ በሠፊው ሊያነጋግረን ይገባል

‹‹ያገሩ ሰርዶ ባገሩ በሬ›› እንደሚባለው ሁሉ በእኛ ጉዳይ ላይ ከኛ ይበልጥ የሚቀርበው አካል የለምና ለተተኪው ትውልድ የወደፊት ሕይወት መሻሻል ሁላችንም እጃችንን እንዘርጋ፣ ታሪክ እንሥራ፣ በጎ አድራጎት በመሥራት ለራሳችን፣ ለልጆቻችንና ለቤተሰባችን እርካታን እንሸምት በማለት እያሳሰብን እስካሁን በነበረው የማህበሩ የ14 ዓመት ጉዞ እና ለተገኘው ስኬት ከፍተኛ ድጋፍ የሰጡትን የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ለጋሽ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በዚህ አጋጣሚ ዕውቅና መስጠት ተገቢ መሆኑን በማመን ማህበሩ የሚከተሉትን ሰዎች ለአብነት ያቀርባል፡፡

 ከሀገር ውስጥ

2.1 ኢንጂነር ብርሃነ አባተ

ኢንጂነር ብርሃነ አባተ ማህበሩ ከተቋቋመበት 1994 ዓ/ም ጀምሮ በግላቸውና በድርጅታቸው በበርታ ኮንስትራክሽን ሃ/የተ/የግ/ማህበር አማካይነት ለማህበሩ የሰጡት ያልተቋረጠ የገንዘብ፣ የማቴሪያልና የሎጂስቲክስ ድጋፍ ማህበሩ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ወሳኝ ነው፡፡ ማህበሩ በተቋቋመበት 1994 ዓ/ም ማግስት ከመስራች አባላት መካከል አንዱ የሆኑት ኢንጂነር ሥዩም ገበየሁ አሜሪካ ከሚገኘው ኢንተርናሽናል ቡክ ባንክ ጋር በመነጋገር የሃያ /20/ ኮንተይነር መጽሓፍት ማህበሩ በዕርዳታ እንዲገኝ በማድረጋቸው በከፍተኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚገባው ድጋፍ ሲሆን ምንም ዝግጅት ባልተደረገበር ሁኔታ ይህን ያህል ዕርዳታ መገኘቱን የተገነዘቡት ኢንጂነር ብርሃነ ዕርዳታውን ተቀብሎ ለማሰራጨት ድርጅታዊ አቅም እንደሚያስፈልግ በመረዳት ከግል ድርጅታቸው ሁለት ትላልቅ አዳራሾችንና ቢሮዎችን ለማህበሩ በነጻ በመስጠት የማይረሳ ውለዋል፡፡ አሁንም ላለፉት 13 ዓመታት ማህበሩ በሕንጻዎቹ እየተገለገለ ይገኛል፡፡ማህበሩ ለሕንጻዎቹ ኪራይ መክፈል ቢኖርበት ኖሮ ብር7,020,000 ወጪ ማድረግ ይጠበቅበት ነበር፡፡ በመሆኑም ማህበራችን ኢንጂነር ብርሃነ አባተን በተገልጋዮቹ የኢትዮያ ሕጻናት ስም የላቀ ምስጋናችና  ያቀርብላቸዋል፡፡

2.2 ክቡር ዶ/ር፣ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ

ማህበሩ የተነሳለትን ዓላማ እንዲሳካ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉት ግለሰቦችና ድርጅቶች መካከል ክቡር ዶ/ር፣ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ እና ድርጅታቸው ኃይሌና ዓለም ኃ/የተ/የግ/ማህበር ናቸው፡፡  የኢትዮያ የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማህበር መስራች አባል ሲሆኑ አንድ ዘመናዊ ክፍል ያለኪራይ በነጻ እንድንገለገልበት መመፍቀድ ድጋፍ አበርክተዋል፡፡ በመሆኑም ማህበሩ በተገልጋዮቸቹ ስም ለክቡር ዶ/ር፣ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴና ለድርጅታቸው ያለውን አድናቆትና አክብሮት ይገልጻል፡፡

2.3 ኢንተርናሽናል በጎ አድራጎት ድርጅቶች

የማህበሩ  እንቅስቃሴ ዘርፈ ብዙ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በዋናነትም ለ International Book Bank (IBB, USA), Books For Africa (BFA, USA) Book Aid International (BAI, UK), Computer Aid International (CAI, UK), Better World Books (BWB, USA), African Universal African Peoples Foundation (UAPO, USA) and HELP – Education Ethiopia (Loretta Foundation, France) እንዲሁም ውጭ የሚኖሩ የኢትዮያ ዲያስፖራ ማህበራት Bethany Negash Memorial Foundation Inc. (Bethany Foundation, USA), Society For The Transfer of Educational Expertise and Resources For Ethiopia (STEERE, Canada) EKTTS (USA OFFICE), ሠፊ የማቴሪያል ዕርዳታ ባይጨመርበት ኑሮ አሁን የተገኘው ውጤት ይገኛል ተብሎ የሚገመት አልነበረም፡፡ በመሆኑም የማህበሩን የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ራዕይ በመጋራትና በመደገፍ ላደረጉት ከፍተኛ የማቴሪያል ዕርዳታ ሁሉንም በዚህ አጋጣሚ ማመስገን ይወዳል፡፡ የሰጡትንም ድግፋ እንደሚከተለው እንጠቅሳለን፡፡

ተራ ቁ

ዝርዝር

 

የተለገሰው የኮንተይነር ብዛት

የመጽሐፍት/ኮምፒውተር ብዛት

1

Books                              

80

1,755,000

2

Computers                                                 

 

29

7,928

3

Medicals

 

2

89,985

4

Medical Teaching Material & Supply                                    

6

  Various

Total

117

Worth $ 53,372,263.00

 

 

 
የማህበሩን ራዕይ በመደገፍ ምክር በመስጠት፣ ሃሳብ በማካፈል፣ አቅጣጫ በማሳየት፣ ዓላማችንን በማስተዋወቅ፣ በአጠቃላይ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ለደገፉን ድርጅቶች፣ ማህበራት፣ ግለሰቦች ማህበሩ ከፍ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡

ማጠቃለያ

የሀገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት መሠረቱ ኅብረተሰቡ ራሱ በመሆኑ ለሀገራችን ዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማሰባሰብ በሚያደርጉት ጥረት ባለው አቅም በገንዘብ፣ በማቴሪያል፣ በሎጂስቲክስ፣ በምክርና በሃሳብ ሊደግፋቸውና ሊያጠናክራቸው ይገባል፡፡ የሌሎች ሀገሮች ልምድ የሚያሳየውም ይኽው ነው፡፡ ስለሆነም በሀገራችን የሚታየውን የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ክፍተት ለማጥበብ ማህበሩ በሚያደርገው ጥረት ከጎናችን እንድትሰለፉ የአክብሮት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

“ለዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በጋራ እንስራ”

 

አድራሻ

ቂርቆስ ክ/ከተማ፣ ወረዳ 05 የቤት ቁ. 190

ስልክ ቁ 0114665728/29

ፋክስ 251-116627886

E-mail: ektts@ethionet.et

Website:  ektts.org.et

ከደህነት ሁሉ አስከፊው የአዕምሮ ድህነት ነው ስለዚህ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋ!!!!

 

Comments